
ባሕር ዳር፡ ግንበት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ፓርቲዎችም ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን መምረጥ እንዲችል በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚሠሯቸውን ዕቅዶች፣ ፕሮግራሞች፣ እጩዎች እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅም ማኅበረሰቡ የራሡን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ለምርጫው ስኬታማነት ደግሞ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች ማኅበር እስከታችኛው ቀበሌ ድረስ በአደረጃጀት ምርጫው ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ያልጋ ወርቁ ሴቶች የመምረጥ እና የመመረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በምርጫ ሂደት ሴቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከአሥተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የሴቶች ማኅበር አባላት በነጻነት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የምርጫውን ሂደት ከሚያውኩ የትኛውም እንቅስቃሴ ራሳቸውን በማራቅ እና ባለመተባበር ሕገ ወጥ ተግባራትን ሲመለከቱ ደግሞ ለሕግ አካላት መረጃ መስጠት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
