ካርድ የሥልጣን ምንጭ በመኾኑ አንድም ድምፅ መባከን የለበትም !

6
🗳️🇪🇹
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዜጎች በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚኖራቸውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት ዋነኛው መሣሪያ የምርጫ ካርዳቸው ነው።
የምርጫ ካርድ የዜጎች የሉዓላዊ ሥልጣን ምንጭ በመኾኑ ድምጻቸውን ወደ ሥልጣን የሚቀይሩበት የውክልና ሰነድ ተደርጎም ይወሰዳል። በምርጫ ሂደት መሳተፍ አንድ ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ባለቤት መኾኑን የሚያረጋግጥበት አንዱ መንገድ ነው።
የአንድ ጊዜ ምርጫ ካርድ ለዓመታት የሚዘልቅ ውጤት እና ጠቀሜታ አለው። ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላም “በዚህ መንግሥት ምስረታ ላይ እኔም ድምፅ አለኝ” የሚል በተመረጠው መንግሥት ላይ የባለቤትነት ስሜትን ይፈጥራል።
ዜጎች ካርዳቸውን ሳይጠቀሙ ማባከን ማለት ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ያለባቸውን ግዴታ አለመወጣት ማለት ነው።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ሕዝብ የወሰደውን ካርድ በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ገልጸዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እመቤት ከበደ ካርድ ማውጣት ብቻውን ለምርጫው ስኬታማነት ግብ አይደለም ብለዋል። መራጮች ካርዳቸውን በጥንቃቄ ይዘው በዕለቱ ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ በመስጠት ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
እንደ ፓርቲም ለአባላቶቻቸው እና ለደጋፊዎቻቸው ቀደም ካሉት ጊዜ ጀምሮ ሰፊ ግንዛቤ ሲፈጥሩ እንደቆዩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አሥተባባሪ ኃይለማርያም ብርሃኑ በርካታ ሕዝብ የምርጫ ካርድ እንዳወጣ ሁሉ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አንድ ካርድ ዋጋ ያላት በመኾኑ መባከን የለባትም ብለዋል። ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ የምርጫ ካርዱን በአግባቡ በመጠቀም በዕለቱ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በመምረጥ የዜግነት ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
# አሚኮ # ምርጫ_2018 #ኢትዩጵያ#
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleበምርጫ ሂደት የተከለከሉ ሕጎችን መጣስ ምን ያስቀጣል?
Next article“ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፍጠር ጥሩ ዕድል አለ” ዶናልድ ትራምፕ