
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን የተቀሰቀሰው ግጭት ዳፋ ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ በርካታ ሀገራት ላይ አርፏል። አሜሪካ እና ኢራንም ጦርነቱን በማቆም የዓለምን የንግድ መስመር በዘላቂነት ለመክፈት የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ነው።
ፍራንስ 24 የዜና ማሰራጫ በማለዳው ይዞት በወጣው ዘገባው ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ስምምነት የመፍጠር ከፍተኛ ዕድል እንዳለ ገልጸዋል። ቴህራን ለዋሽንግተን አዲስ የሰላም ሃሳብ ልካለች። ይህንን ተከትሎ ትራምፕ በኢራን ላይ ሊሰነዘር የነበረውን ጥቃት አግደዋል።
የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት ወቅት አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የነዳጅ ማዕቀብ ለማንሳት ተስማምታለች። በተጨማሪም የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራን ሰሞኑን ለአሜሪካ ባቀረበችው የሰላም ሃሳብ ውስጥ ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ የታገዱ ገንዘቦች እንዲለቀቁ እና የተጣለው እገዳ እንዲያበቃ የሚሉ ጥያቄዎች መካተታቸውን ለኢራኑ ይፋዊ የዜና ወኪል (ኢራና) ተናግረዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ዋናው ግባቸው የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር መገደብ እንደኾነ አስታውቀዋል። ለአሁኑ ሊደረግ የነበረው ጥቃት ለጊዜው መሰረዙንም አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ አጥጋቢ ስምምነት ካልተገኘ ጦሩ ዝግጁ እንዲኾን መታዘዙን አስታውቀዋል። ጦርነቱ በማንኛውም ቅጽበት በከፍተኛ ደረጃ ሊጀመር ይችላልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
