ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩ ግለሰቦች በምርጫ ለመወዳደር ዕውቅና ካገኙ በኋላ በሕግ ከተከለከሉ ቦታዎች ውጭ የመቀስቀስ መብት አላቸው
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር አብዬ ካሳሁን የተከለከሉ ቦታዎች ለአንዱ ተፍቅደው ለሌሎች የተከለከሉ አለመኾናቸውን ተናግረዋል። በተፈቀዱ ቦታዎች የቅስቀሳ ሥራቸውን የመተግበር አቅም ልዩነት ግን ሊኖር ይችላል ነው ያሉት።
ተወዳዳሪዎች ሊያሳምኑት የሚፈልጉትን ሕዝብ በመሠብሠብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት፣ ፖስተር ለጥፎ መልዕክት በማስተላለፍ፣ ሰላማዊ በኾነ በማንኛውም መንገድ ሁሉ ቅስቀሳቸውን ማካሄድ ይችላሉ ብለዋል።


ለምርጫ ቅስቀሳ የተከለከሉ ቦታዎች

ቤተክርስቲያን

መስጊዶች

ወታደራዊ ካምፖች እና ፖሊስ ጣቢያዎች

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች

ትምህርት ቤቶች

ሕዝብ የዕለት ከዕለት ግብይት በሚፈጽምባቸው ቦታዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።

በምርጫ ሂደት የተከለከሉ ቦታዎች ላይ የተቀመጠውን ሕግ መጣስ ምን ያስቀጣል?
ሕግ ሲወጣ መብትን፣ ኀላፊነትን እና ግዴታን ያስቀምጣል ያሉት ዳይሬክተሩ ተጥሶ ሲገኝ ተጠያቂነት እንደሚኖር ነው ያመላከቱት። ተጠያቂነቱ እንደ ሕግ ጥሰቱ ዓይነት ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሚደረግም አመላክተዋል።

በማታለል እና ሁከት በሚፈጥር ኹኔታ በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እንቅፋት መፍጠር ከአንድ ዓመት እስከ ሦሥት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 148 ላይ መመላከቱንም ገልጸዋል።

ማሳመን ሲገባ ያለ አግባብ ተጽዕኖ በማሳደር መቀስቀስም እንደ ኹኔታው ክብደት ከአንድ እስከ ሦሥት ዓመት እሥራት ያስቀጣል ነው ያሉት።

የመንግሥትን ሀብት እና ሥልጣንን ለምርጫ ቅስቀሳ ያለ አግባብ መጠቀም ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት እንደ ኹኔታው የሚያስቀጡ የሕግ ድንጋጌዎች እንዳሉም ተናግረዋል።

የምርጫ ቁሳቁስ ላይ ጉዳት ማድረስ (ፖስተር መገንጠል፣ አቅጣጫ ጠቋሚዎችን ማንሳት እና መሰል ጥፋቶች) ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣም ተናግረዋል።

የሥነምግባር ጥሰት ከተፈጠረ ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በምርጫ ቦርድ የተሰጠው የአየር ሰዓት ወይም የገንዘብ ድጋፍ እገዳ፣ ከፍተኛ ጥፋት ሲፈጸም እጩ ተወዳዳሪውን ፓርቲ (ግለሰብ) ከውድድር የመሠረዝ አሥተዳደራዊ እርምጃም ይወሰዳል ብለዋል።
ከሕግ ተጠያቂነት አኳያ አተገባበሩ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ካሉ ደግሞ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓቶች እንዳሉ ነው ያስገነዘቡት።