“ጀግንነትን ተላብሰን የአማራን ሕዝብ ከማንኛውም ጥቃት እየጠበቅን ነው ” የአድማ መከላከል ሠራዊት

7
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ የ36ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ሠራዊት አባላት ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ዝግጁነታቸውን በመጠበቅ ማንኛውንም የላቀ ወታደራዊ ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሠራዊቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ ሕገ ወጥ ታጣቂ ቡድኑን በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላም የማስፈን ተልዕኮውን በድል አድራጊነት እየተወጣ ነው።
የአማራን ሕዝብ ዕረፍት ለመንሳት እና ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚዳዳቸውን ታሪካዊ ጠላቶችም ኾኑ በሀገር ውስጥ የተፈለፈሉ የጥቅም አደሮችን አደብ ለማስገዛት ሠራዊቱ የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ የመፈፀም ሙሉ ብቃት እና ቁርጠኝነት እንዳለው አባላቱ ገልጸዋል።
የ36ኛ ሻለቃ አዛዥ ምክትል ኮማንደር በሪሁን ውዱ “ጀግንነትን ተላብሰን፣ ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጠን፣ የአማራን ሕዝብ ከማንኛውም ጥቃት እየጠበቅን እንገኛለን፤ የሚሰነዘርብንንም ጥቃት በመመከት የክልላችን እና ሀገራችንን ሰላም ለማስፈን ግዳጃችንን በጀግንነት እየተወጣን ነው” ብለዋል።
የሚሰጣቸውን ግዳጅ በዕውቀት እና በጥበብ ለመፈጸም በአካልም ሆነ በሥነ ልቦና ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሻለቃው በተሰማራበት የውጊያ ቀጣና ሁሉ ውጤታማ መኾኑን አስረድተዋል።
ደብረ ማርቆስ ከተማን መነሻ በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በተከናወነ ኦፕሬሽን በርካታ የታጠቁ ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል። ጠላት ይዟቸው የነበሩ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ተደርጓል ነው ያሉት።
የሻለቃው ወታደራዊ ወትሮ ዝግጁነት ከፍተኛ በመኾኑ በጠላት ላይ በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ ተችሏል ብለዋል። የኦፕሬሽን ሥራዎች በሙሉ ፖሊሳዊ ሥነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ እየተከናወኑ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ሠራዊቱ ወታደራዊ ተልዕኮውን ከመወጣት ባለፈ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ እና የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ሕዝባዊነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ ለሠራዊቱ ወሳኝ መረጃዎችን በመስጠት እና አጋዥ በመኾን አብሮ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በዚህ የተቀናጀ ጥረት በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን በነፃነት ማከናወን መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የሻለቃው አባላት ዋና ሳጅን መኳንንት አዲሴ እና የዲሽቃ ተኳሹ ሳጅን ብርሃኑ ዓለምነህ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ ከአጋር የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ከአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ይህንኑ ተጋድሎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleሥልጣን የሚገኘው በካርድ ብቻ ነው።
Next articleበምርጫ ሂደት የተከለከሉ ሕጎችን መጣስ ምን ያስቀጣል?