
በሀሳብ የበላይነት ብቻ በማመን በቅስቀሳ ወቅት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚያስተላልፉት መልዕክት ለብጥብጥ እና ለሁከት የሚዳርግ እንዳይኾን በጥንቃቄ ሊመራ ይገባል ብለዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲም ይህንኑ መመሪያ መሠረት አድርጎ በምረጡኝ ቅስቀሳዎቹ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር ተስፋሁን ዓለምነህ ስኬታማ ምርጫ የሚካሄደው በምርጫ ቦርድ የተቀመጡ ሕጎችን እና ደንቦችን በአግባቡ አክብሮ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
መብትን ለመጠቀም ግዴታን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በቅስቀሳ ወቅት አንዱ የሌላውን ስም በማያጎድፍ መልኩ መንቀሳቀስ የሠለጠነ ፖለቲካ መገለጫ መኾኑንም አንስተዋል።
አዴኃንም ይህንን መሠረት በማድረግ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ባስቀደመ መልኩ ለምርጫው እየተዘጋጀ መኾኑን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
S
