በምዕራብ ጎንደር ዞን ለምርጫው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቅቋል።

7
🇪🇹
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመጭው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ 113 የምርጫ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መኾናቸውን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ አስታውቀዋል።
የዘንድሮውን ምርጫ ለየት የሚያደርገው ዝግጅቱ በራሱ በማኅበረሰቡ ቀጥተኛ ባለቤትነት እና ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ የተመሠረተ መኾኑ ነው ብለዋል።
ነዋሪው ሥልጣን የሚገኘው በሕዝብ ድምጽ ብቻ መኾኑን በመረዳት፣ በራሱ ፈቃድ የምርጫ ካርዱን ወስዶ የድምጽ መስጫውን ዕለት በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል ነው ያሉት።
እንደ አቶ እያሱ ገለጻ ሠራተኞች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ያለምንም ተፅዕኖ እና ጫና፣ የሚወክላቸውን አካል በነፃነት መምረጥ እንዲችሉ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተከናውኗል።
ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እጩዎቻቸውን እና ምልክቶቻቸውን ይዘው፣ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ እያካሄዱም ነው።
የምርጫው ሂደት በሰላም እንዲጠናቀቅ የዞኑ አሥተዳደር ከጸጥታ አካላት እና ከዞኑ ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም ዋና አሥተዳዳሪው ጠቁመዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የአሥተዳደር አካላትም ለምርጫ ቦርድ መሪዎች እና አሥፈጻሚዎች የሚያስፈልጉትን የቢሮ፣ የመጋዘን፣ የትራንስፖርት እና የሥልጠና አዳራሽ አቅርቦቶችን በሙሉ ማሟላታቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየምርጫ ካርዱን በንቃት የወሰደው ማኅበረሰብ ምርጫው ላይም መድገም አለበት።
Next articleየምርጫ ቅስቀሳ የሕዝብን ደኅንነት ያስቀደመ የሀሳብ መድረክ ይሁን!