
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ ለማድረግ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በምሥራቅ ጎጃም ዞንም ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ገልጸዋል።
ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ሙሉ ዕውቀት እና ግንዛቤ ኖሮት በነጻነት ይወክለኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ እንዲችል ሰፊ የግንዛቤ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በዞኑ በሚገኙ 15 የምርጫ ክልሎች እና 1 ሺህ 26 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን የተናገሩት አሥተዳዳሪው ለምርጫ ዝግጁ የኾነ የማኅበረሰብ ክፍል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ለማስቻል መራጩ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ፕሮግራም እና ማኒፌስቶ መሠረት ያደረገ ማብራሪያ እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።
ገዢውን ፓርቲ እና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ወክለው የቀረቡ ዕጩዎችን ለኅብረተሰቡ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
በዞኑ ስምንት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉም አንስተዋል።
ኅብረተሰቡ የምርጫ ካርዱን በስፋት እንደወሰደው ሁሉ በመጭው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ላይም የሚፈልገውን ፓርቲ በንቃት እንዲመርጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
