
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላበራቶሪዎችን አቅም በማጠናከር የፀረ-ተሕዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአቅም ግንባታ ላበራቶሪ ዳይሬክተር ዳንኤል መለሰ የመድኃኒት መላመድ ችግር በዓለም ላይ ለዜጎች ሞት የዘጠኝ ከመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም በየዓመቱ በርካታ ዜጎች ለህልፈት ይዳረጋሉ ነው ያሉት። ችግሩ ከፍተኛ በመኾኑ ሰፊ ዓለም አቀፍ ትኩረት እና ጣልቃ ገብነት ይሻል ብለዋል።
ለችግሩ መባባስ ዋናው ምክንያት ያለ ላበራቶሪ ምርመራ መድኃኒት የማዘዝ ልማድ እንደኾነ ነው የገለጹት። ይህንን ክፍተት ለመፍታት ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ የላበራቶሪ ማስፋፊያ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ከመሠረታዊ እስከ ከፍተኛ የበሽታ አምጪ ተሕዋስያን ወይም የሰውን ልጅ ማንነት በሴል ውስጥ በሚገኙ የጄኔቲክ ቁሶች ደረጃ የሚመረምር (ሞለኪውላር) ላበራቶሪዎችን የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት።
በሁለት ሆስፒታሎች ውስጥ የማይክሮ ባዮሎጂ ላበራቶሪ እየተገነባ ነው፤ የሞለኪውላር ላበራቶሪም በመተማ ሆስፒታል እየተሠራ ነው ብለዋል።
የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ እንደኾነም አንስተዋል። በሰው ኃይል፤ በቁሳቁስ እና በመዋቅር አቅምን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በዓለም ባንክ እና በአፍሪካ ሲዲሲ ፕሮጀክት አማካኝነት በክልሉ ከአምስት በላይ የክልል ማዕከላዊ ላበራቶሪዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
አቅምን ለማሳደግ የተጀመሩት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መኾናቸውንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከኢንስቲትዩቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
