“ኢትዮጵያ የመረጃን ዋጋ በመረዳት በሠራችው ሥራ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

5
አዲስ አበባ: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን በምንገኝበት ዘመን የሀገራት ድንበር ብቻ ሳይኾን መረጃቸውንም በመመንተፍ ጭምር ሉዓላዊነት እየተደፈረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ከውጭ ተጽዕኖ የተላቀቀ የራሷን የመረጃ ሉዓላዊነት የመጠበቅ ጉዞ ላይ ትገኛለች።
ከዚህ ቀደም በሌሎች አካላት በሚደገፉ እና በተበታተኑ የመረጃ ቋቶች ላይ የነበራትን ሙሉ ጥገኝነት ለመቅረፍ ባሳየችው ከፍተኛ ቁርጠኝነት ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
የዚህ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ማብሰሪያ መርሐ ግብር “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” በሚል መሪ መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የመረጃን ዋጋ በመረዳት በሠራችው ሥራ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የተጀመረውን ሀገራዊ የመረጃ ሉዓላዊነት እና የፓሊሲ ነፃነት ጉዞን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት።
ይህ ስኬታማ ሥራ መረጃዎች በኢትዮጵያ ልጆች እንዲሠበሠቡ እና እንዲተነተኑ በማድረግ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የፖሊሲ ነፃነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ሀገራዊ የመረጃ ሥርዓቱ በውጭ ድጋፍ ጥገኝነት ላይ የቆየ እና የተዓማኒነት ጥያቄዎች የሚነሱበት እንደነበር አንስተዋል።
ከዚህ ለመላቀቅ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም እና የ10 ዓመታት የልማት ዕቅድ አፈጻጸም መከታተል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል።
የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት፣ የቱሪዝም መረጃ እና የቢዝነስ ድርጅቶች ቆጠራ ለዚህ የሚጠቀሱ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ፣ በዲጂታል ሥርዓት በማዘመን፣ ለመረጃ ልማት ኢንቨስት በማድረግ የመረጃ ተኮር ፖሊሲ አመራር እና ውሳኔ ሰጭነትን ማረጋገጥ መቻሉን አመላክተዋል።
“የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” በሚል መሪ መልዕክት በተጀመረው በዚህ መርሐ ግብር ለዘርፉ ስኬት ያበቁ ተሞክሮዎችን የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።
ዘጋቢ- ኢብራሒም ሙሀመድ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በእንጅባራ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የብልጽግናን ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next article“የራስን መረጃ በሀገር ልጅ መሰብሰብ እና መተንተን ትልቅ ሀገራዊ ኩራት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)