
እንጅባራ: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በእንጅባራ ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ፤ የትራፊክ ኮምፕሌክስ፤ የገበያ ማዕከል፤ የደም ባንክ እና የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጭ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ነው የጎበኙት።
ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት መደበኛ በጀት፣ በዓለም ባንክ ብድር እና ከኅብረተሰብ ተሳትፎ በተገኘ ሀብት ነው እየተገነቡ የሚገኙት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እየተገነቡ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ጽዳት እና ውበት የሚጠብቁ፤ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የብልጽግናን ጉዞ የሚያፋጥኑ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መኾናቸውን ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደኾኑም ገልጸዋል።
የገበያ ማዕከል ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የፍጥነት ችግር የታየባቸው ፕሮጀክቶች ደግሞ ያለባቸውን ችግር ቀርፈው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
