በአማራ ክልል ለ860 ሺህ ተጋላጭ ወገኖች የሚውል የ1 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ!

2
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ተጋላጭ ወገኖችን ለመደገፍ፤ የማገገሚያ እና የማቋቋሚያ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ይፋ ባደረገው ፕሮጀክት አተገባበር ላይም በወርልድ ቢዥን ኢትዮጵያ የአማራ ክልል ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቴዎድሮስ አባተ እና የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን የስምምነት ፊርማ አከናውነዋል።
የወርልድ ቢዥን ኢትዮጵያ የአማራ ክልል ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቴዎድሮስ አባተ ፕሮጀክቱ 860 ሺህ የሚጠጉ ተጋላጭ ወገኖችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ 120 ሺህ በላይ የሚኾኑት ሕጻናት መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የተገኘ የ1 ነጥብ 15 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በጀት እንደተያዘለትም ገልጸዋል።
አራት ፕሮጀክቶች (የአደጋ ምላሽ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች፣ የረጅም ጊዜ ድጋፍ፣ በሕጻናት ላይ ያተኮሩ ተግባራት) ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
በዚህም በአማራ ክልል የሚገኙ 6 ዞኖች እና 16 ወረዳዎች ላይ የሚኖሩ ተጋላጭ ወገኖች ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት። ለፕሮጀክቶች ተፈጻሚነት የክልሉ መንግሥት፣ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ከዚህ በፊት ሲያደርጉ እንደነበረው ሁሉ እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን ክልሉ በተለያዩ ጸጋዎች የታደለ ቢኾንም በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ወርልድ ቢዥን ኢትዮጵያ ደግሞ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያቶች እያገዘ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ከዛሬው ስምምነት በፊት የ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ስምምነት ማድረጉንም አስታውሰዋል። ይህም በጋራ የመሥራት ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዛሬ በተደረገው የፕሮጀክት ስምምነት የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የምግብ፣ የውኃ አቅርቦት እና ንጽሕና አጠባበቅ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ብልጽግና የገባውን ቃል የፈጸመ፣ የልማት ሥራዎችን ያስፋፋ፣ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፓርቲ ነው ” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article”የበደልነውን ሕዝባችንን ለመካስ የሰላም አማራጭን ተከትለናል” ሰላምን የተቀበሉ ታጣቂዎች