
ከሚሴ: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም አማራጭን ከተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ወደሰላም የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ለአሚኮ እንዳሉት ለሕዝብ እንታገላለን ብለን ጫካ ገብተን የነበረ ቢኾንም ዕውነታው ግን መልሰን ሕዝባችንን እያሰቃየን ቆይተናል ብለዋል።
“ሕዝባችንን ስናሳድድ እና ስናሰቃይ ነበር” ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎቹ አሁን ላይ ግን ሲበድሉት የቆዩትን ሕዝብ ለመካስ ቆርጠው ወደሰላም መምጣታቸውን አረጋግጠዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም ካውንስል ጸሐፊ አህመድ ጁሀር ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በማድረግ በርካታ ሰዎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ እያደረጉ መኾኑን ጠቅሰው አሁንም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ የሰላምን አማራጭ ለተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ አካላትን አመስግነዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን በማደራጀት ወደልማት ለማስገባት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
ለሰላም የተከፈተው በር አሁንም ክፍት መኾኑን ገልጸው ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ሕዝቡን ነፃ አወጣለሁ ብሎ የሚንቀሳቀሰው ኀይል መልሶ ሕዝብን እያሰቃየ እና እየጎዳ ይገኛል ብለዋል።
የሰላምን አማራጭን የተቀበሉ ወንድሞች አሁንም በጫካ የቀሩ ወንድሞቻቸው ወደሰላም እንዲመጡ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
