
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም ክልላዊ የእስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ በባሕር ዳር ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።
የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮጀክቱ አሥተባባሪ ይበልጣል ወንድምነው እንደ ሀገር የአቮካዶ ምርትን በመጠን እና በጥራት ለማምረት እና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን የሚያስችል ልምድ አናሳ እንደነበር አንስተዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው የገለጹት። ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል ለ15 ዓመት የሚቆይ ሲኾን ሀገሪቱ ከ5 ዓመት በኋላ በአቮካዶ ምርት ኤክስፖርት ከሚያደርጉ የአፍሪካ ሀገራት በቀዳሚነት እንድትሰለፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በክልሉ ከ500 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አንስተዋል። ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ አርሶ አደሮችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ናቸው።
ፕሮጀክቱ በተለይም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ያሉት ኀላፊው በአማራ ክልል ባሉ 11 ዞኖች በ39 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚኾንም ገልጸዋል።
ከሚመረተው የአቮካዶ ምርት 50 በመቶው ለኤክስፖርት የሚውል ሲኾን 40 በመቶው የሚኾነው ምርት ደግሞ ለምግብ እና ሥርዓተ ምግብ የሚውል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
