
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላበራቶሪዎችን አቅም በማጠናከር የፀረ-ተሕዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ቅኝት እና መከላከል ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ መድኃኒትን የተላመዱ ጀርሞችን መለየት የሚችሉ ላበራቶሪዎች ቁጥር 16 ብቻ ናቸው ብለዋል። እነዚህም ላበራቶሪዎች ደረጃቸው ዝቅተኛ በመኾኑ እና በተደጋጋሚ ሥራ በማቋረጣቸው ሐኪሞች ያለ ላበራቶሪ ምርመራ እና ሕክምና ለመስጠት መገደዳቸውን ጠቁመዋል።
ይህ አሠራር በሆስፒታሎችም ውስጥ በደም ኢንፌክሽን ምክንያት የበርካታ ሕጻናት ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት እየኾነ መምጣቱን ነው የጠቁሙት።
በተጨማሪም ተህዋስያን መድኃኒቶችን መላመዳቸው የታዘዙ መድኃኒቶች እንዳይሠሩ በማድረግ ሕሙማንን ለሞት እና ለከፍተኛ ሥቃይ እየዳረገ እንደኾነም ገልጸዋል።
ይህንን አደጋ ለመግታት ዛሬውኑ በላበራቶሪ ሥርዓት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እና ዘርፉን የጤና ሥርዓቱ ዋና አካል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። አስቸኳይ ትኩረት እና የተቀናጀ የመከላከያ ሥራም ወሳኝ መኾኑን ነው የጠቆሙት።
በመድረኩ የተገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማይክሮባዮሎጂ መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባዬ ገላው ባክቴሪያዎች በሕይወት ለመኖር ሲሉ መድኃኒቶችን በአጭር ጊዜ የመላመድ ከፍተኛ ባሕሪ አላቸው ብለዋል። ይህንን ተግዳሮት ለይቶ ለማወቅ ደግሞ የማይክሮባዮሎጂ ላበራቶሪዎች ወሳኝ እንደኾኑ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ላበራቶሪዎቹ የሚገባቸውን ያህል ትኩረት አላገኙም ነው ያሉት።
በመኾኑም ይህንን ዘርፍ ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
