
ደብረማርቆስ: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረማርቆስ ከተማ አምራችና ሻጭን በቀጥታ ማገናኘት የሚያስችል የገበያ ማዕከል ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀምሯል።
የከተማ አሥተዳደሩ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮሴፍ መለሰ የገበያ ማዕከሉ ዘመናዊ ግብይትን የሚፈጥር እና ተወዳዳሪነትንም የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ አርሶ አደሮች እና አምራች ኢንዱስትሪዎች በቀጥታ ምርታቸውን ለተጠቃሚ የሚያደርሱበት በመኾኑ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የገበያ ማዕከሉ ከተማ እና ገጠርን የሚያስተሳስር ሸማችንም በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ሥራው የሦሥተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን ማስቀረት እና የኑሮ ውድነትን መቀነስ ዓላማው ያደረገ በመኾኑ ተቋሙን ለታሰበለት ዓላማ ለማዋል እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በምረቃ መርሐግብሩ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ .ር) የአካባቢውን የአርሶ አደሮች ምርት ወደ ገበያ በማቅረብ በኢንዱስትሪ የሚቀርቡ ምርቶችንም በቀጥታ ለሸማች በማድረስ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ በመኾኑ አገልግሎቱን በቶሎ እንዲጀምር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ በከተማ አሥተዳደሩ እና በክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነባ መኾኑም ታውቋል፡፡
#አሚኮ_ዜና #የገበያ_ማዕከል #ደብረማርቆስ_አማራክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
