🗳️በምርጫ ወቅት የማኅበረሰቡን የመረጃ አጠቃቀም ንቃተ-ሕሌና ማሳደግ ይገባል።

3

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች በነፃነት ድምፃቸውን የሚሰጡበት ሂደት ቢኾንም በምርጫ ወቅት ከሀሰተኛ መረጃዎች መጠበቅ ያስፈልጋል።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር አበራ የኔወርቅ (ዶ.ር) ጊዜው የቴክኖሎጂ ማደግን ተከትሎ የሐሰተኛ መረጃዎች ቅርጽ እና ይዘት እየተቀያየረ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ መኾኑን ገልጸዋል። ይህንን ችግር ለመከላከልም የማኅበረሰቡን የመረጃ አጠቃቀም ንቃተ-ሕሌና ማሳደግ እንደሚገባም ነግረውናል።

ዕውነተኛ መረጃን የሚያጣሩ ተቋማትን ማበራከት ቀዳሚ መፍትሔ መኾኑንም አብራርተዋል። ​በተለይም ምርጫ ዜጎች በነፃነት ድምጽ የሚሰጡበት ሂደት ቢኾንም፤ በዚህ ወቅት የሚፈጠሩ የፈጠራ ወሬዎችን ለመግታት ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ነው የተናገሩት።

ለዚህም እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎች ታማኝ የሚዲያ አውታሮች የሚሰጧቸውን መረጃዎች እና ድረ-ገጾች መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

​ዶክተር አበራ በዚህ ወቅት በማኅበረሰቡ የሚናፈሱ ወሬዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ የሚያጋልጥ እና የመከላከል ሥራውን የሚመራ ግብረ-ኀይል ማደራጀት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

​ስለ ምርጫው አጠቃላይ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ መረጃዎችን መጠቀም ያስፈልጋልም ነው ያሉት። ​ማኅበረሰቡ እርግጠኛ ያልኾነባቸውን መረጃዎች ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ራስን ከሐሰተኛ የመረጃ አውታሮች መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
በአጠቃላይ በምርጫ ወቅት የአሉባልታ ወሬዎችን ለመግታት እውነተኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባሞ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #አማራክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመረጃ ሉዓላዊነት 🇪🇹 ኢትዮጵያ በራሷ መረጃ ላይ ተመስርታ እንድትወስን አስችሏታል።
Next articleበደብረ ማርቆስ ከተማ አምራችና ሻጭን በቀጥታ ማገናኘት የሚያስችል የገበያ ማዕከል ሥራ ጀመረ።