“ሕዝብ የፈለገውን ተወካይ እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታ አለ” ጥላሁን ደጀኔ

5
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በአማራ ክልል ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የፖለቲካ ፓቲዎችም ሕዝብ ውክልናውን በነጻ ፈቃድ ይሰጣቸው ዘንድ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በአዳራሽ ስብሰባ እና በዓደባባይ ሰልፍ ሀሳባቸውን እየሸጡ ይገኛሉ።
በደቡብ ጎንደር ዞንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብ ይመርጣቸው ዘንድ የተለያዩ ነጻ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ነው።
በዞኑ በ17 የምርጫ ክልሎች እና በ1 ሺህ 371 የምርጫ ጣቢያዎች ሕዝቦች ይወክለኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ቁርጠኛ ኾነው እየተንቀሳቀሱ ነው።
በዞኑ 51 የብልጽግና ተወካዮች እና 78 የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች በምርጫው ለመሳተፍ እና የሕዝብ ውክልናን ለማግኘት በስፋት እየተንቀሳቀሱ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በዞኑ ሕዝብ በነጻነት ወጥቶ የሚፈልገውን ተወካይ በክልልም ኾነ በፌዴራል እንዲመርጥ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የዞኑ ሕዝብ ምርጫ የዴሞክራሲ መሠረት እና መብትን በሚገባ የመጠቀም አንዱ ማሳያ እንደኾነ በመረዳቱ በምርጫ ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሕዝቡ እያሳየ ያለው መልካም ባሕሪ እና ሕግ አክባሪነቱ ዴሞክራሲ እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡
ገዥው ፓርቲም ኾነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት አንጻር እየተመካከሩ የምርጫ ቅስቀሳውን እያካሄዱ እንደኾነም ዋና አሥተዳዳሪው አረጋግጠዋል፡፡
ምርጫ እንዳይካሄድ ሢሠሩ እና ሲቀሰቅሱ የቆዩ ጸረ ሰላም ኃይሎች አሁንም ትንኮሳቸውን ባያቆሙም ዞኑ ለምርጫው ዝግጁ ኾኖ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ሕዝብ ሴራቸውን በመረዳቱ ሀሳባቸውን ውድቅ በማድረግ ሕልማቸውን እያመከነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት እንደሚያስፈልግ በመረዳት ለምርጫው ልዩ ትኩረት እየሠጠ ከዞኑ አሥተዳደር ጋር እየሠራ ስለመኾኑም አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ የሚገነባውን የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክት የዲዛይን ግምገማ አካሄደ።
Next article“ሀገርን የሚያሻግር ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል” የጻግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች