የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ የሚገነባውን የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክት የዲዛይን ግምገማ አካሄደ።

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባሕር ዳር ከተማ የሚያስገነባው ሁሉን አካታች የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት ፕሮጀክቱን የዲዛይን ግምገማ አካሂዷል።

ፕሮጀክቱ የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እና በላቀ ሁኔታ ለመስጠት እንዲሁም አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገ ሁሉን አካታች የፍትሕ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ የያዘ እንደኾነ በዕለቱ ተነስቷል።

የፕሮጀክት ዲዛይኑ በኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተሠራ እንደኾነም ተገልጿል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ቴወድሮስ ምህረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የቱሪም ሚኒስትር ድኤታ ስለሽ ግርማ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ጠበቆች፣ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው አርክቴክቶች፣ የጥበብ ባለሙያዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የዲዛይን ግምገማው ተካሂዷል።

ከኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መሪዎች እና ሲኒየር አርክቴክቶች ጋር በመኾን መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ናቸው። ከግምገማ መድረኩ ጠቃሚ ግብዓቶች እንደተገኙበት ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ዲዛይኑን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ እና ሌሎች የቅደመ ዝግጅት ተግባራትን በመሥራት የፕሮጀክት ግንባታው የሚጀምረበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በሙዚየሞቿ ታሪኳን እየገለጠች ነው።