
ሁመራ፡ ግንቦት 9/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገር ዳር ድንበር መጠበቅ እና ለሉዓላዊነት መረጋገጥ ዋጋ ለከፈለው የሚሊሻ ኀይል ተገቢው ክብር እየተሰጠ መኾኑን የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ገልጿል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፤ በቤት ሞሎ ከተማ አሥተዳደር ተከብሯል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን የዘመቻ ዋና መምሪያ ኀለፊ ይታገስ አምባቸው የሶማሊያን ወረራ በመመከት የሚሊሻው ሚና ከፍተኛ መኾኑን አስረድተዋል።
ሚሊሻ በዚያድ ባሬ ወረራ ወቅት ሀገርን ከመፍረስ የታደገ የሀገር ባለውለታ መኾኑንም አቶ ይታገስ ገልጸዋል። ለዚህም የሚገባውን ክብር እና ዕውቅና በመስጠት የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት ሚሊሻ ለከፈለው ውድ ዋጋ ተገቢው ክብር ሳይሰጠው መቆየቱን አስታውሰው ይሄ በዓል ለሚሊሻ ለተሰጠው ክብር ማሳያ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የሚሊሻን 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ማክበር ለዞኑ ድርብ ድል መኾኑን ያነሱት ደግሞ የዞኑ ሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ ሻምበል እሸቴ አወቀ ናቸው።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ነጻ ከወጣ በኋላ የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት ከፌዴራል እና ከክልሉ የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ሚሊሻ ዋጋ እየከፈለ ነውም ብለዋል።
የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት የተቀናጀ እና የተደራጀ የሚሊሻ ኀይል መገንባት በትኩረት እየተሠራበት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የአካባቢው ሚሊሻ የዞኑን እና የሀገሪቱን ዳር ድንበር በመጠበቅ ትልቅ ዋጋ እየከፈለ ነው ሲሉ የቤት ሞሎ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አለበል አነጋው ገልጸዋል። በተለያዬ ጊዜ ውድ ሕይወታቸውን ለከፈሉ የሚሊሻ አባላትም ተገቢው ካሳ መሰጠቱንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዘመናት ሚሊሻ ተገቢውን ዕውቅና አለማግኘቱን የበዓሉ ተካፋይ የሚሊሻ አባላት ተናግረዋል። በዓሉን ማክበር ለሚሊሻ የተሰጠውን ክብር የሚያሳይ በመኾኑ ለሚሰጣቸው ግዳጅ ተነሳሽነትን እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
