
ጎንደር :ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ የልማት ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ ገለጹ።
ፓርቲው ስንዴ በማምረት ከተረጅነት ነጻ ለመሆን በሰነቀው የልማት መስመር በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተሻለ ምርት መመረቱን ገልጸዋል።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ በዞኑ ባለፉት የበጋ ወራት 29ሽህ 200 በላይ የስንዴ ልማት ተመዝግቧል።ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን የተገኘው ውጤት የፓርቲውን የመሪነት ሚና የሚያሳይ ነው።
ሌላኛው በዞኑ እየታየ ያለው የልማት መስክ በዞኑ የተለያዩ ከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ነው። የኮሪደር ልማት በቆላ ድባ፣በአባ ጊዎርጊስና በሌሎች የዞኑ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ አወቀ ሳውቀዋል።
የኮሪደር ልማት ከተሞችን ከማስዋብ ባሻገር የስራ ባህልን የለወጠ መሆኑንም አንስተዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትና የፋሲል አብያተ መንግስታት ጥገና ሌላኛዎቹ የብልጽግና ፓርቲ የልማት ቱሩፋቶች መሆናቸውን የገለጹት አቶ አወቀ ብልጽግና የልማት ሥራዎችን ጀምሮ መጨረስ መለያው የሆነ ፓርቲ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ከተጀመረ አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ፓርቲው ለፕሮጀክቱ በሰጠው ትኩረት ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አረጋግጠዋል። የመስኖ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በምስራቅ ደንቢያና አካባቢው ብቻ ከ17ሽህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም ያለው መሆኑን አሳውቀዋል።
ፓርቲው ባለፉት አምስት ዓመታት በሰጠው ትኩረት የተመዘገበው ዋና ተግባራት ውስጥ በትምህርት፣በጤናና መሰል ማህበራዊ ዘርፎች የታየው ለውጥ ተጠቃሽ መሆኑንም ዋና አስተዳዳደሪው ገልጸዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ550ሽህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ አወቀ ከ87ሽህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አስረድተወል።
“ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት እየተጋ ያለውን ብልጽግና ፓርቲ መምረጥ ልማትን ማስቀጠል ነው” ሲሉም ማህበረሰቡ ፓርቲውን በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲመርጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቆላ ድባ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የመወዳደሪያ ምልክት ማስተዋወቅ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ከቆላ ድባ ከተማና ከምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ፓርቲውን ወክለው በመጭው ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተወል።
ሀይሉ ማሞ
