
ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ በመገኘት የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ባቡር ፕሮጄክትን ዳግም ሥራ አስጀምረዋል።
ፕሮጄክቱ የማኅበረብ ትስስርን በመፍጠር፣ የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ እና የንግድ ሥርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አለው።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና የደረቅ ወደብ መዳረሻ ናት ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ለፕሮጄክቱ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው የፕሮጄክቱ መጀመር የሕዝቡን ጥያቄ የመለሰ መኾኑን ተናግረዋል።
የፕሮጄክቱ መቋረጥ ማኅበረሰቡ አሳዝኖ እንደነበር የገለጹት ከንቲባው ዳግም ወደ ሥራ መግባቱ በነዋሪዎች ዘንድ ደስታ ፈጥሯል ነው ያሉት። ምርቶችን ለማቅረብ የንግድ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ፕሮጄክቱ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል። ፕሮጄክቱን በመጠበቅ፣ ሠራተኞቹን በመደገፍ አካባቢውን ለሠራተኞች ምቹ በማድረግ ዞኑ እና ነዋሪዎቹ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳስበዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የሕዝብን እንቅስቃሴ በማሳለጥ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር ፕሮጄክቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ፕሮጄክቱ በደቡብ ወሎ በርካታ ቦታዎችን እንደሚሸፍን አንስተው የማኅበረሰቡን ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል።
ለአካባቢው ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
#አሚኮ #ኮምቦልቻ #ባቡር መሥመር #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
