
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር ከትናንት በስቲያ ባካሄደዉ ስምሪት አራት የጽንፈኛዉ ቡድን አመራሮችን ጨምሮ በ31 የውጭ ጠላቶችን ተልዕኮ አስፈፃሚ የሀገር ዉስጥ ባንዳዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። 40 የሚኾኑትን ቁስለኛ አድርጓል፤ 3ቱን ደግሞ ማርኳል።
የክፍለ ጦሩ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ምሥራቅ መንበር ክፍለ ጦሩ በሀሙሲት፣ አንበሳሚ፣ አርብገበያ፣ ምሥራቅ እስቴና አንዳቤት በተባሉ ቦታዎች በመግባት ጽንፈኛዉን በመምታት አካባቢዉ ከነበረበት የፀጥታ መደፍረስ ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ የማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።
ኮሎኔሉ እንዳሉት ሰሞኑን በምሥራቅ እስቴ ወረዳ ገንዳ ጠመም ወረዳ በተደረገዉ ኦፕሬሽን 31 የጽንፈኛ አባላትን በመደምሰስ፤ ሦስት ፅንፈኛ መማረካቸዉን እና 40 ማቁሰላቸዉን በመግለፅ የተለያዩ መሳሪያዎችንም መማረካቸዉን ተናግረዋል።
ፅንፈኛዉ አመራሬ ናቸዉ ብሎ ሲጠራቸዉ የነበሩ ማስቴ ቢሆን የተባለ የመቅደላ ብርጌድ ዘመቻ መሪ፣ ተሻገር አውለው ሥልጠና እና ምልመላ መሪ፣ አማኑኤል አስናቀ እና የመቅደላ ብርጌድ ሕዝብ ግንኙነትን ጨምሮ በሠራዊቱ ብርቱ ክንድ መደምሰሳቸዉ ተገልጿል።
ሠራዊቱ የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅ ግዳጁን ከክልሉ የፀጥታ ኃይል እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ተላላኪዉን ፅንፈኛ እግር በእግር እየተከታተለ የመደምሰሱን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሌተናል ኮሎኔል ምሥራቅ መንበር አስታውቀዋል። መረጃው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምሥራቅ ዕዝ ነው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
