
ጎንደር :ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቆላ ድባ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የመወዳደሪያ ምልክት ማስተዋወቅ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ከቆላ ድባ ከተማና ከምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ፓርቲውን ወክለው በመጭው ምርጫ የሚወዳደሩ በምክትል ርእሰመስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የደንቢያ አንድ ምርጫ ክልል የክልል ምክር ቤት እጩ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፣የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊና የክልል ምክር ቤት እጩ አቶ ፋሲል ሰንደቁ ፣ወይዘሮ በላይነሽ ገበያው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርእሰመስተዳደር ማዕረግ የአስተዳድር ክላስተር አስተባባሪና የደንቢያ አንድ ምርጫ ክልል የክልል ምክር ቤት እጩ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በቀጣይ ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂደዋል።
ዶክተር አማኑኤል የደንቢያ ህዝብ በችግር ጊዜ ሀገሩን የሚጠበቅ፣በሰላም ጊዜ ደግሞ የልማት አርበኛ መሆኑን አስታውሰዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫና መዳረሻ የሚወስን በመሆኑ ህዝቡ ሰላምን ሊያረጋግጥ፣ልማትን ሊያፋጥን ይችላል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲና እጩ እንዲመርጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለሀገር ልማትና ሰላም እየተጋ የሚገኝ መሆኑንም አሳውቀዋል።
ፓርቲው ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በመቀየር
ህዝብ ልማት ላይ ብቻ ትኩረቱን እንዲያደርግ አበክሮ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ፓርቲው በበጋ ስንዴና በሌሎች የልማት ዘርፎች እያስመዘገበ ያለውን ውጤቶች የበለጠ ለማሳደግና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሰባተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ህዝቡ በእውቀት ተመስርቶ ብልጽግናን እንዲመርጥ መልእክት አስተላልፈዋል ።
ያለ ህዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥ ልማት አይኖርም ያሉት ዶክተር አማኑኤል ሰላሙ የተረጋገጠ፣ደህንነቱ የተጠበቀ ፣በልማቱ የበለጸገ ሀገር ለመገንባት በቀጣይ እንደሚሰራም አሳውቀዋል።
የሀገር መጻእይ እድል ብሩህ እንዲሆን ብልጽግናን መምረጥ እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሀይሉ ማሞ
