🚆”የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገቢያ የባቡር ፕሮጄክት ወደ ሼል መግባት መንግሥት የሕዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ያሳየ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

4

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ በመገኘት የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያን የባቡር ፕሮጄክት ዳግም ሼል አስጀምረዋል።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር መሠረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ስለሽ ካሳ
የአዋሽ -ኮምቦልቻ-ሀራ ገቢያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት በሰሜን ቀጠና ያሉ አካባቢዎችን ከጅቡቲ እና ከአሰብ ወደብ ጋር የሚያገናኝ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መኾኑን ተናግረዋል።

የሀራ ባቡር መሼመር በቀጣይ ከሚሠራው ወረታ – መተማ የባቡር ፕሮጀክት የሚያስተሳስር ነው ብለዋል። 392 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ከመቋረጡ በፊት ከሀገር ውጭ በመጡ ባለሙያዎች ይሠራ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ይሠራል ነው ያሉት።

በመጀመሪያ ዙር የማስጀመሪያ ሥራ የዝግጅት ምዕራፍ የሠራተኞችን ማረፊያ ካምፖችን የማዘጋጀት፣ ሠራተኞችን ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር ተከናውኗል ነው ያሉት።

በቀጣይ በሁለት ዓመታት እንደሚጠናቀቅም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
ፕሮጀክቱ የማኅበረሰብ ትስስርን ለመፍጠር፣ ምርት እና ግብዓትን በፍጥነት ለማንቀሳቀስ እና የንግድ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ በሰሜኑ ጦርነት በደረሰበት ውድመት፣ በተቋራጩ በተፈጠረ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች ተቋርጦ እንደነበር አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት ትኩረት አማካኝነት በሁለት ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።

ይህ ፕሮጄክት ዳግም ወደሥራ መግባቱ መንግሥት የሕዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል።

ምርትን በሰላማዊ መንገድ ማጓጓዝ ካልተቻለ ውጤታማ መኾን አይቻልም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ይህ ፕሮጄክት መጀመሩ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

የፕሮጄክቱን ደኅንነት በመጠበቅ በኩል የክልሉ መንግሥት ሢሠራ መቆየቱን ገልጸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🇪🇹”ብልጽግና ፓርቲ አፍሪካዊ ተምሳሌት የኾነች ሀገር የመገንባት ራዕይ ይዞ እየሠራ ነው” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ
Next article“ብልጽግና ፈተናዎችን ተቋቁሞ ልማትን እያረጋገጠ ያለ የትውልድ ፓርቲ ነው” አቶ ኃይሌ አበá‰