ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጎዴ የሚገነባውን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ጎበኙ።

5

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ናይጀሪያዊው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በሶማሌ ክልል ጎዴ የሚገነባውን ማዳበሪያ ፋብሪካ ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመሆን በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ለማቋቋም ትልቅ የባለድርሻ ስምምነት ተደርጎ እንደነበር አንስተዋል። በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ደግሞ የፕሮጀክቱን ግንባታ በይፋ ስለመጀመሩም ገልጸዋል።

ይኽ ሥራ ከመሠረተ ልማት ግንባታም በላይ ነው፤ በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የኢንዱስትሪ እድገት እና በኢኮኖሚ ራስ የመቻል ጥረት ውስጥ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ኢንቬስትመንት ነው ብለውታል።

የማዳበሪያ ፋብሪካው በሚጠናቀቅበት ወቅት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ያጎለብታል፤ ከውጭ በሚገባ ማዳበሪያ ላይ ያለውን ጥገኝነት ይቀንሳል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮቻችንን ይደግፋል ነው ያሉት። ለኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራም አዳዲስ እድሎችን እንደሚከፍት አመላክተዋል።

“ዛሬ ማለዳ ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን በጎዴ ተገኝቼ ሥራው የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም የፕሮጀክት ስፍራውን ጎብኝቻለሁ” ብለዋል። በመላው የፕሮጀክቱ ስፍራ የሚታየው የሥራ ሂደቱ ፍጥነት አበረታች ነው፤ ይኽን ግዙፍ እና እጅግ ጠቃሚ ሀገራዊ ፕሮጀክት ለመፈፀም ያለውን ቁርጠኝነት እና ትብብር በሚያንፀባርቅ ሁኔታ በተለያዩ የፕሮጀክቱ ክፍሎች ያሉት ግንባታዎች በእቅዳችን መሠረት እየተጓዙ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article📢 የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ 5 ሺህ ሠራተኞችን ይፈልጋል።
Next articleየፓኪስታን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሞህሲን ናቂቭ ቀውሱን ለማርገብ ቴህራን ገብተዋል።