
ደሴ: ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የፓርቲውን የምርጫ ምልክት እና ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በስፖርታዊ መርሐ ግብር ለሕዝብ አስተዋውቋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ አቢ ባስተላለፉት መልእክት ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በመደመር የሚያምን በመኾኑ የጋራ ስፖርታዊ ውድድሮችን ያበረታታል ነው ያሉት። በቀጣዩ ምርጫ ወጣቱ ትውልድ ብልጽግናን በመምረጥ ተስፋ ሰጪ ለውጦችን እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
”ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
ስፖርት የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ቁልፍ ጉዳይ መኾኑን በማመላከት ብልጽግና ፓርቲ ለዘርፉ መጠናከር በልዩ ትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ስፖርት መተባበርን፣ አንድነትን እና መተጋገዝን የሚጠይቅ መኾኑን የተናገሩት ዋና አፈ ጉባኤዋ ብልጽግና ፓርቲም የመደመር መርሕን የሚተገብረው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መኾኑን ጠቁመዋል።
ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል የሕዝቡ ድምፅ ወሳኝ በመኾኑ ፓርቲውን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
