🗳️ ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሥራው መጀመር ያለበት ከቤት እና ከጎረቤት ነው።

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች በነጻነት እና በፈቃደኝነት ተወካዮቻቸውን ወይም መሪዎቻቸውን የሚመርጡበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ ነው።

በዚህ የምርጫ ሂደት የእናቶች ንቁ ተሳትፎ እጅግ መሠረታዊ ነው።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ እናቶችም ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ነግረውናል።

ወይዘሮ ሰይዳ ሙሐመድ የምርጫ ካርዳቸውን በእጃቸው ይዘው ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ መኾናቸውን አጫውተውናል። ወይዘሮ ሰይዳ በተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚቀርቡ አማራጭ ሀሳቦችን በአግባቡ እየተከታተሉ መኾናቸውንም አንስተውልናል።

“ሀገር ማለት እናት ናት”፤ ሀገር ሰላም ሲኾን ነው ትውልድ የሚኖረው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ሀገርን መጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ስኬታማ ምርጫ እንዲካሄድ “ሰላም ለልሴ” ብለን በማሰብ የድርሻችንን እንወጣለን” ብለዋል።

ሌላኛዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እናት ገነቴ ታደሰ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ድምጽ ለመስጠት ካርዳቸውን ይዘው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በምርጫው ቀን “ይህ መሪዬ ነው” ለማለት በዝግጅት ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ሰላም ለሴቶች እጅግ አስፈላጊ መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሥራው መጀመር ያለበት ከቤት እና ከጎረቤት ነው” ብለዋል።

በምርጫ ካርድ የቀጣዩን የአምስት ዓመት የሀገር ዕጣ ፈንታ ለመወሰን መዘጋጀት ይገባል ነው ያሉት።

“ሰላም በእጃችን ነው” ያሉት እናቶቹ ሁሉም እናቶች በየአካባቢያቸው ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

#አሚኮ #እናቶች #ምርጫ2018 #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article✈️ የረጅም ዓመታት ጥያቄ ብስራት ይዞ ብቅ አለ፤ ታሪካዊ በረራም ተከናወነ 🇪🇹
Next article“ስፖርት የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ቁልፍ ጉዳይ በመኾኑ ብልጽግና ፓርቲ ለዘርፉ መጠናከር በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ