✈️ የረጅም ዓመታት ጥያቄ ብስራት ይዞ ብቅ አለ፤ ታሪካዊ በረራም ተከናወነ 🇪🇹

11

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለበርካታ ዓመታት በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያውን ታሪካዊ የሙከራ በረራ በትላንትናው ዕለት እውን አድርጎ ብቅ ብሏል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ተመስገን ተድላ
የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመር የከተማዋን የኢንቨስትመንት እና የንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃው ገልጸዋል።

በረራው መጀመሩ የባለሀብቶችን ውድ ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ ፕሮጀክቶቻቸውን በቅርበት ለመከታተል እና የውጭ ኤክስፐርቶችን ድጋፍ በቀላሉ ለማግኘት ያስችላል ነው ያሉት።
ኢንቨስትመንቶችን የውጭ ዜጎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና ኤክስፐርቶች በቅርበት መጥተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ዕድል የሚሰጥ መኾኑንም አንስተዋል።

የምርት እና ምርታማነት ጥራትን በማሳደግ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመኾን የነበሩ ችግሮችን እንደሚፈታ ገልጸዋል። አምራቾች ምርታቸው ሳይበላሽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ እንዲያደርሱም ትልቅ መሠረተ ልማት ኾኖ እንደሚያገለግል ነው ያስረዱት።

ይህ የአውሮኘላን ማረፊያ ጥያቄ የደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ሕዝብ ለረጅም ጊዜ በአንድ ድምፅ ሲያነሳው የነበረ ታላቅ ጥያቄ ነበር ብለዋል።

ቀደም ሲል ኅብረተሰቡ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ አደገኛውን እና ረጅሙን የዓባይ ሸለቆ ለመሻገር ይገደድ ነበር፤ ይህም በሕይወት እና በንብረት ላይ የአደጋ ስጋት እንደነበር ነው የተናገሩት።

ጥያቄው በመመለሱ ሕዝቡ እጅግ መደሰቱን እና ይህም ለውጥ ለከተማዋ ዳግም መወለድ መኾኑን ኀላፊው አብራርተዋል። በተለይም መደበኛ በረራው ሲጀመር በከተማዋ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና አገልግሎቶች ጥራታቸውን እንዲያሻሽሉ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ደብረ ማርቆስ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ እጅግ ምቹ እና ሰፊ አቅም ያላት ከተማ በመኾኗ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የበረራ ማስጀመሪያው ላይ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

✈️#ደብረማርቆስ #አውሮፕላን-በረራ #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጄክትን ጎብኝተዋል።
Next article🗳️ ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሥራው መጀመር ያለበት ከቤት እና ከጎረቤት ነው።