ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጄክትን ጎብኝተዋል።

4

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የደብረ ማርቆስን አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጄክትን እና የሙከራ በረራን ጎብኝተዋል።

የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው። ዛሬ ደግሞ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በተገኙበት የሙከራ በረራ አካሂዷል። የሙከራ በረራውም ስኬታማ ነበር።

የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው የዓመታት የሕዝብ ጥያቄን የመመልስ ነው። የአውሮፕላን ማረፊያውን እስከ ከተማ የሚያገናኝ መንገድም እየተገነባ ነው።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች የአውሮፕላን ማረፊያው የሙከራ በረራ መጀመሩ እና ግንባታው በጥሩ ደረጃ ላይ በመኾኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል። መንግሥት ለጥያቄያቸው ለሰጠው መልስም ምስጋና አቅርበዋል። ለከፍተኛ መሪዎችም የካባ ስጦታ አበርክተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ እየተጠናቀቀ በመኾኑ እና የመጀመሪያውን የሙከራ በረራ በማድረጋችን ደስ ብሎኛል ብለዋል። የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ለደብረ ማርቆስ እና ለአካባቢው ሕዝብ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። ይህ በመሳካቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

የሙከራ በረራ ሲያደርግ በሕዝቡ ላይ የነበረው ደስታ የሚያስደንቅ መኾኑንም አንስተዋል።

የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆና ተመርቆ ወደ መደበኛ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፋብሪካው የልማት አርበኝነታችንን የምናሳይበት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ