
ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ሰባተኛ መደበኛ እና ስምንተኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባቤውን በደጀን ከተማ አካሂዷል።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ እየተጠናቀቀ በመኾኑ እና የመጀመሪያውን በረራ በማድረጋችን ደስ ብሎኛል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ለደብረ ማርቆስ እና ለአካባቢው ሕዝብ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ተናግረዋል። ይህ በመሳካቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
በዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ሥር እየተገነባ የሚገኘው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጄክትን እንደ ትልቅ አደራ እንመለከተዋለን ነው ያሉት።
በነበሩ ችግሮች በተፈለገው ልክ ሳይሄድ ቆይቷል፤ አሁን ግን በተሻለ ደረጃ ላይ ነው፤ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ እንደማይመለስ ተመልክተን አረጋግጠናል ብለዋል።
ፕሮጄክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የማድረግ ኀላፊነት ተጥሎብናል ነው ያሉት። ፕሮጄክቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫችን ነው ብለዋል።
ባለ አክሲዮኖች ሥራው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ፕሮጄክቱ የልማት አርበኝነታችንን የምናሳይበት ነው ብለዋል። የአካባቢው መሪዎች ሥራውን በትኩረት እንዲከታተሉም አሳስበዋል።
ትልቅ አደራ አለብን፤ ይሄን አደራ በአግባቡ እንወጣ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
