
እንጅባራ: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የጥናት እና ምርምር ኮንፈረንስ አካሄደ።
ኮንፈረንሱ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሳይበር ደኅንነት እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ነው። ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራን የምርምር ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) “በዲጂታል ክህሎት ያልታገዘ የሀገር እድገት እና ተወዳዳሪነት ጉዞ አዝጋሚ ይኾናል” ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት የተቀመጡ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ዕቅዶችን በመንደፍ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል::
ከ84 በመቶ በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች ነጻ የኮደርስ ሥልጠና እንዲከታተሉ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ኮንፈረንሱ ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለባለድርሻ አካላት የምርምር ግኝቶችን ለማጋራት ያግዛል ነው ያሉት።
ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የተያያዙ ዕድሎችን እና ተግዳሮቶችን ለመፈተሽ የሚያግዝ መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
