“ጊዜ ዘነጋሽ፤ ጊዜም አስታወሰሽ”

4

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ንጉሥ ተክለሃይማኖት የነገሡብሽ፤ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ የከተሙብሽ፤ ሊቃውንቱ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የማይነጥፉብሽ፤ ማር እና ወተት የሚቀዳብሽ፤ ነጭ ጤፍ በእርጎ የሚበላብሽ ደብረ ማርቆስ ኾይ እንዴት ከርመሻል?

አንቺ በበዓድ ሀገር የነበሩትን ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን አክብረሽ የተቀበልሽ፤ አሳምረሽ ያስተናገድሽ፤ ደግሰሽ ያሳረፍሽ፤ በደስታ እና በሀሴት በእልፍኝሽ ያሰነበትሽ፤ ስንቅ አስቋጥረሽ የሸኘሽ፤ በመራቂ አባቶች የታደልሽ፤ በመካሪ እናቶች የተባረክሽ፤ በአስተዋይ ልጆች የተመላሽ፣ ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት ጀግኖች የመከሩብሽ፤ ቃል ኪዳን ያሠሩብሽ፤ ልዑል ራስ እምሩ የከተሙብሽ፣ ቅዱስ ማርቆስ ግርማን የሰጠሽ፤ ከስሙ ስምሽን የወረስሽ፤ አብማ ማርያም የምትባርክሽ የደጋጎቹ ከተማ እንደምን ባጅተሻል?

ከዓመታት በፊት የንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ አውቶሞቢል የተጓዘችብሽ፤ ከብዙዎቹ ቀድመሽ የሰማይ ጢያራ የተመላለሰብሽ፤ ማር እና ቅቤን በሰማይ ጢያራ የጫንሽ፤ ከዓመታት በፊት የሰለጠንሽው፣ በመካከልም የተዘነጋሽው የንጉሥ ተክለሃይማኖት መናገሻ ኾይ እንደምን ኖረሻል ?

ዘመን አነሳሽ፤ ዘመን እና ዘመናውያንም ዘነጉሽ፤ አስቀድሞ የነበረሽን ነሱሽ፤ የሥልጣኔሽን ማሳያ አስቀሩብሽ፤ አንቺም በትዕግሥት ለዓመታት ጠበቅሽ፤ ትዕግሥትሽ እና አስታዋይነትሽም መልሶ የአንቺን ዘመን አመጣልሽ፤ ለዓመታት የናፈቅሽ፤ በትዕግሥት የጠየቅሽው፤ በማስታዋል ያቀረብሽው፤ በተስፋም የጠበቅሽው ጥያቄሽ ተመለሰልሽ፤ ስለ አንቺ ሁሉም ደስ ይለዋልና እንኳን ደስ ያለሽ?

ድሮ ማሩን በአቁማዳ አሥረው፤ ቅቤውን አስተካክለው፤ ከወተት የነጣውን ጋቢ እና ኩታ ደርበው፣ ቀጭን ዘንጋቸውን ይዘው በሰማይ ጢያራ (በአውሮፕላን) የተመላለሱት የጎጃም መኳንንቶች፤ ያማረውን ለብሰው፤ እንደ ማለዳ ጀንበር አብርተው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ የሚጓዙት የጎጃም እናቶች ያስቀኑ ነበር።

ታዲያ ጊዜው ተቀይሮ በደብረ ማርቆስ ሰማይ ላይ የሚያንዣብበው አውሮፕላን ቀርቶ፤ አየር ማረፊያውም በዳዋ ተውጦ እነዚያ ዓባይን በሰማይ የሚሻገሩት፤ በአውሮፕላን ማር እና ቅቤ የሚጭኑት ደጋጎች የለመዱትን አጥተው ለዓመታት በዝምታ ቆዩ። የዓባይን በረሃ በትዕግሥት ወጡ ወረዱ። ዳግም ጊዜው እስኪመለስ ታገሱ።

አዲስ ሥጡን አላልንም፤ የነበረንን ግን መልሱልን እያሉ ሲጠይቁ ኖሩ። ከዓመታት ጥየቃ በኋላ እነኾ የደብረ ማርቆስ ጥያቄ ተፈትቶ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቶ የሙከራ በረራ ጀመረ። አውሮፕላን ናፍቆት የነበረው የደብረ ማርቆስ ሰማይም ከአውሮፕላን ጋር ተገናኘ። አሁን እንደዚህ ይባላል:-

“ከእንግዲህስ ወዲያ ሀገር አለፈለት
ቅቤው እና ማሩ በሰማይ ሄደለት” እየተበላ ይዜማል። ከዓመታት በፊት ቅቤ እና ማር በአውሮፕላን የሚጭኑት እነዚያ ደጋጎች የቀድሞው ጊዜ ተመልሶላቸዋል። ከእንግዲህ የዓባይን አቀበት አይታገሉትም፤ የዓባይን ቁልቁለት አይደክሙለትም፤ ወደ ታች እየተመለከቱት በሰማይ ይሻገሩታል እንጂ። እንግዲህ እነዚያ አሳምረው የሚለብሱት፤ ተጊጠው የሚወጡት የጎጃም እናቶች እና አባቶች በየብስ አይንከራተቱም፤ ከበረሃው ጋር አይታገሉም። በአየር ይሻገራሉ እንጂ።

የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ መጀመር ከትራንስፖርት ባሻገር ነው። ይህ ግንባታ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው። ትርጉሙም በርካታ ነው።

ከዚህ በኋላ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከተማ በጉብኝዎች ትታሰሳለች፤ የጎጃም ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ይገለጣሉ፤ ከእንግዲህ በአውሮፕላን ትራንስፖርት ምክንያት ከአካባቢው ርቀው የነበሩ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ደብረ ማርቆስ ያቀናሉ።

በደብረ ማርቆስ እና አካባቢውም መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈስሳሉ። የአካባቢው ኢኮኖሚ ይነቃቃል። ደብረ ማርቆስም በታሪኳ ልክ ታድጋለች። ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓመታት በኋላ ወደ ደብረ ማርቆስ የሙከራ በረራ ሲያደርግ የከተማዋ ነዋሪዎች በደስታ ተቀብለውታል።

የዓመታት ጥያቄያቸው ተፈትቷልና ደስታቸውን በእልልታ ገልጸዋል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዓባይ ስሚንቶ ፋብሪካ የድካም ፍሬውን ሊሰጥ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው” አቶ መላኩ አለበል
Next articleበዲጂታል ክህሎት ያልታገዘ የሀገር እድገት አዝጋሚ ነው።