“የዓባይ ስሚንቶ ፋብሪካ የድካም ፍሬውን ሊሰጥ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው” አቶ መላኩ አለበል

5

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ሰባተኛ መደበኛ እና ስምንተኛ አስቸኳይ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባቤውን በደጀን ከተማ አካሂዷል።

በጉባኤው ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ መላኩ አለበል፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ጉባኤው በተለያዩ ርእሰ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ሥር እየተገነባ የሚገኘው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጄክት በጥሩ ሂደት ላይ መኾኑን ገልጸዋል። ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ወደ ኋላ እንዲመለስ አንፈልግም፤ በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።

የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ደምስ ተሻገር ጉባዔው በፕሮጄክት ጽሕፈት የተደረገው ባለ አክሲዮኖች፣ የተቋማት ኀላፊዎች እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የፋበሪካው ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ በአካል ተመልክተው የተሟላ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ከባለድርሻ አካላት ለሚጠብቁት ድጋፍ በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማሳለፍ እንዲችሉ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር መኾኑንም ገልጸዋል።

ባለአክሲዮኖች የቅድሚያ መብታቸውን ተጠቅመው ለተፈቀደው ተጨማሪ ካፒታል ቃል እንዲገቡ እና ለገዙት አክሲዮን ክፍያ እንዲፈጽሙም አስገንዝበዋል።

የአካባቢው ማኅብረሰብ እንደ እስካሁኑ በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

በውል ስምምነታቸው መሠረት የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካን ለማጠናቀቅ እና ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ዓባይ ስሚንቶ ፋብሪካ ከውስብስብ ችግር አልፎ ከዚህ ደርሷል ብለዋል። ፕሮጄክቱ ተናግሮ የመፈጸም እና ተጀምሮ የመጨረስ ምሳሌ እየኾነ መኾኑን አንስተዋል።

በትብብር እና በቅንጅት በተያዘለት ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ምርት እንዲገባ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ መላኩ አለበል የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ የድካም ፍሬውን ሊሰጥ በጥሩ ደረጃ ላይ መኾኑን ገልጸዋል።

ጉባዔውን በዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት ማድረጋችን ግንባታው የደርሰበትን ደረጃ ለመገንዘብ ዕድል የሰጠ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ኢትዮጵያ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ የምታደርገውን የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያግዝ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ ትብብር ስኬታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የዓባይ ሲሚንቶ ፕሮጀክትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን ፋይናንስ ማሰባሰብ ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የኩባንያው የሥራ አመራር አባላት፣ የቴክኒክ አማካሪዎች እና ተቋራጩ በትጋት እንዲሠሩም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጎበኙ።
Next article“ጊዜ ዘነጋሽ፤ ጊዜም አስታወሰሽ”