ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጎበኙ።

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደጀን ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና የዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ መላኩ አለበል፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ( ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ ( ዶ.ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር ሥር እየተገነቡ ከሚገኙ የልማት ሥራዎች መካከል አንደኛው ነው።

የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር አስራት ኪዳኑ ዓባይ ሲሚንቶ ትልቅ አቅም ያለው መኾኑን ገልጸዋል።

ፕሮጄክቱ 45 በመቶ አፈጻጸም ላይ መድረሱንም አስታውቀዋል። ተቋራጩ እና አማካሪው ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው መኾናቸውን ተናግረዋል። በሰላሳ ወራት ለማጠናቀቅ ውል እንደተያዘለት የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ ተቋራጩ ግን በሃያ አራት ወራት ለማጠናቀቅ እየሠራ ነው ብለዋል።

ፕሮጄክቱ ሲጠናቀቅ ለአማራ ክልል እና ለመላው ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መኾኑንም አንስተዋል። ፕሮጄክቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተገነባ የሚገኝ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረገበት እና ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የተፋሰስ ልማት ወደተሻለ የልማት ከፍታ እየተሸጋገረ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next article“የዓባይ ስሚንቶ ፋብሪካ የድካም ፍሬውን ሊሰጥ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው” አቶ መላኩ አለበል