የ30 ዓመቱ ናፍቆት ተፈታ፣ ለደብረ ማርቆስ ከተማ ዳግም ልደት ኾነ!

9

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለብዙ ዓመታት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያውን ታሪካዊ የሙከራ በረራ ዛሬ በታላቅ ስኬት አስተናግዷል።

የመጀመሪያው የመንገደኞች አውሮፕላን ማረፊያውን ሲረግጥ በስፍራው የነበሩ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በታላቅ ደስታ እና በእልልታ ተቀብለውታል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ መሀሪ ዘውዴ የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎቱ እስከ 1988 ዓ.ም አገልግሎት ሲሰጥ ቢቆይም በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይህ አገልግሎት ከ30 ዓመት በኋላ መመለሱ ጥልቅ ደስታን እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።

የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት ሙከራ መጀመሩ ለደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ማኅበረሰብ ዳግም ልደት ነው ብለዋል።

ይህ አውሮፕላን ማረፊያ ተራ የልማት ግንባታ ሳይኾን የደብረ ማርቆስ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ሕይወት በቀጥታ የሚቀይር ነው ብለዋል።

‎​ሌላኛዋ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ማስተዋል ዳኘ በበኩላቸው የአውሮፕላን መንገዱ አገልግሎት እንዲጀምር የረጅም ጊዜ የሕዝብ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ጥያቄያቸው እውን ኾኖ ዛሬ ደግሞ የሙከራ በረራ በማድረጉ እጅግ መደሰታቸውን አንስተዋል።

የግንባታ ሥራው ተጠናቆ በቀጣይ መደበኛ በረራ ሲጀመር የትራንስፖርት፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በማነቃቃት አይተኬ ሚና እንደሚጫወትም ተስፋ ማድረጋቸውን ነው ያነሱት።

ቀደም ሲል ነዋሪዎች ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ አድካሚውን እና አስፈሪውን የዓባይ በረሃ መንገድ ለመሻገር ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ሳቢያ በርካታ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ጽኑ ሕሙማን ለከፋ እንግልት እና ለሞት ይዳረጉ እንደነበር በቁጭት አስታውሰዋል።

ይህ የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀምር እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በሙከራ በረራው የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የደብረ ማርቆስ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲኾን በቀጣይ እድሳቱ ተጠናቅቆ መደበኛ በረራውን እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

#አሚኮ #ዜና #አውሮፓላን_ማረፊያ #ደብረማርቆስ_አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተማማኝ ኢኮኖሚን ለመገንባት በጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ተደማሪ እመርታ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ‎