ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪዎቹን አስመረቀ።

3

 

ጎንደር ፡ ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 444 የሕክምና ዕጩዎችን አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው ለ41ኛ ዙር በተለያዩ የሕክምና ትምህርት ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ዕጩዎች ነው ያስመረቀው።

ተቋሙ ከመጀመሪያ እስከ ሦሥተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን እንዲሁም በልዩ የትምህርት ዘርፎች ላይ ትኩረታቸውን አድርጎ ሲያሠለጥናቸው የነበሩ ተማሪዎች ናቸው ዛሬ የተመረቁት።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ልጃለም ጋሻው በመርሐ ግብሩ “የተለያዩ ችግሮችን አልፋችሁ ለሀገራችሁ ፈውስ ለመኾን የምትችሉበት ምዕራፍ ላይ ደርሳችኋል፣ መጭው የሥራ ጊዜ የተሠጣችሁን የምትሰጡበት ሲኾን በፍፁም ሰብዓዊነት እና ርህራሄ ኀላፊነታችሁን እንደምትወጡ እተማመናለሁ” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በምረቃ መርሐግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ተመርቆ ወደ ሥራ መግባት በብዙ እየተፈተነ ያለውን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል ትልቅ ግብዓት መኾኑን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት፣ በትክክል ተረድቶ መተግበር ጅግንነት እና ጽናት እንደሚጠይቅም ዶክተር አሸናፊ አንስተዋል።

ሕክምና ሰብዓዊ ግንኙነት ያለው ሥራ መኾኑን ያነሱት ዶክተር አሸናፊ ተመራቂዎች ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለሙያው በማዋል ለሕሙማን ፈውስ እንዲኾኑም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ማርታ አዱኛ

#አሚኮ #ዜና #ምረቃ_የሕክምናትምህርት #ጎንደር_አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየ30 ዓመቱ ናፍቆት ተፈታ፣ ለደብረ ማርቆስ ከተማ ዳግም ልደት ኾነ!
Next article“የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የተፋሰስ ልማት ወደተሻለ የልማት ከፍታ እየተሸጋገረ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ