🏭 ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ዳግም ስኳር ማምረት ጀመረ።

3

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) ​🇪🇹 የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በኢትዮጵያ ካሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ፋብሪካው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ምርት ሳይሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

አሁን ላይ ያጋጠሙት ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተቀርፈውለት በተሟላ መንገድ ስኳር ማምረት መጀመሩን የፋብሪካው ሥራ አሥኪያጅ ባይነሳኝ ዘሪሁን አስታውቀዋል።

የፋብሪካው ዳግም ሥራ መጀመር በጉጉት ሲጠብቀው ለነበረው ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጭምር ደስታን ፈጥሯል ነው ያሉት። ከአካባቢው ማኅበረሰብ በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።

ፋብሪካው ሰፊ የሰው ኀይል እንደሚፈልግ አንስተው አኹን ላይ ግን የሠራተኛ እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል። የሠራተኛ እጥረቱን በተወሰነ ደረጃ ለመሸፈንም የአካባቢው ማኅበረሰብ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።👨‍👩‍👧‍👦💼

በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው የሚፈለገውን ምርት ለማምረት 5ሺህ ሠራተኞችን እንደሚፈልግ አስታውቀዋል። ለዚህም ሥራ የሚፈልጉ ወገኖች ወደ ፋብሪካው መጥተው የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይም ወደ ሙሉ ማምረት አቅሙ ሲሸጋገር ከ23ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ስለመኾኑም ነው የገለጹት።

ፋብሪካው ከነበረበት ችግር ወጥቶ ዳግም ለውጤት እንዲበቃ ድጋፍ ላደረጉት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግስ፣ ለኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩኘ፣ ለጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ቦርድ አባላት፣ ለአካባቢው አመራር እና ማኅበረሰብ ሥራ አሥኪያጁ ምሥጋና አቅርበዋል። 👏

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

#አሚኮ #ዜና #ጣና_በለስ #ስኳር_ፋብሪካ #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየግብርና ምርቶች እና የፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትስስር ይጠናከራል።
Next article“የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተማማኝ ኢኮኖሚን ለመገንባት በጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ተደማሪ እመርታ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ‎