የግብርና ምርቶች እና የፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትስስር ይጠናከራል።

4

 

ባሕርዳር፡ ግንቦት08/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ቢሮ ግብዓት እና ሜካናይዜሽን ዘርፍ የግብርና ውል እርሻ አሠራር ላይ ምክክር እያደረገ ነው።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዴሊበሪ ዩኒቲ ኀላፊ ደረጃው ፈንቴ (ዶ.ር) ክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል። በዚህም ክልሉን የሚያሻግር የ10 ዓመት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

ከተዘጋጀው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስትራቴጅዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ የገበያ ትስስር መፍጠር መኾኑን ጠቅሰዋል።

ክልሉ የገባበት የአርሶ አደር ስጋት የሚባለው የገበያ ስጋት መኾኑንም ጠቅሰዋል። ይህን ሊቀርፍ የሚችለውና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እና ሳይንስ የሚያሳየው ደግሞ የውል እርሻ አሠራር መኾኑን ነው የገለጹት።

የእኛ የግብርና አሠራር የተመሠረተውም በውል እርሻ የማምረት አቅማቸው አነስተኛ የኾኑት አርሶ አደሮች ላይ ነው ብለዋል። ገበያ ተኮር እና ዘመናዊ የኾነ የግብርና ሥርዓት ለማምጣት ደግሞ የገበያ ሥርዓትን ማዘመን እና ማስተሳሰር ይጠይቃል ነው ያሉት።

የክላስተር እርሻ በሰፊው መሥራትንም ይጠይቃል ብለዋል። ክልሉ በተግባር የገባበት የውል እርሻም ይህን የገበያ ችግር ይፈታል በሚል መኾኑን ገልጸዋል።

ክልሉ በቅባት እህሎች ጀምሮ በሰፊው ሌሎችን ምርቶች ወደ ማምረት እየሄደ መኾኑንም አንስተዋል። ይህም ከግብአት አቅራቢዎች እና አምራቾች ባሻገር የውጭ ምንዛሬ በማምጣት ለሀገር እያበረከተ ያለው ሚና ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

የበለጠ እየሠፋ መሄድ ግን ይኖርበታል ነው ያሉት። ፋብሪካ ገንብተን ጥሬ እቃ ከውጭ ልናማትር አይገባምም ብለዋል። የተፈጥሮ ሃብታችን ተጠቅመን የግብርና ሥራን ማስተሳሰር አለብን ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ደግሞ የዛሬው ምክክር የውል እርሻ አሁን ላይ ያለበት ኹኔታ፣ በአስመራቹ እና በአምራቹ ላይ የሚስተዋሉ ሊቀረፉ የሚገባቸው ችግሮች እና ለሌሎች አርሶ አደሮች ለማስፋት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተመከረ በኋላ በቀጣይ የምርት ዘመን ይሄ ሥራ ተግባራዊ እንዲደረግ የጋራ ጥረት ለማድረግ መኾኑን ተናግረዋል።

የውል እርሻ አሠራር ሲተገበር የማያተርፍ የለም ያሉት ኀላፊው ከሁሉም በላይ መጠቀም አለበት ተብሎ የሚታሰበው አነስተኛው አርሶ አደር መኾኑን ነው የጠቀሱት። አነስተኛው አርሶአደር በሚቀርብለት የሙያ ድጋፍ እና የቴክኖሎጅ አቅርቦት ምርት እና ምርታማነቱን በማሻሻል ገበያውን እና የኑሮ ደረጃውን ያሻሽላል ተብሎ እንደታሰበም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

#አሚኮ_ዜና #የውል_እርሻ #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላማችን እየጠበቅን የሀገርን ብልጽግና እናስቀጥላለን” የሰቆጣ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎች
Next article🏭 ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ዳግም ስኳር ማምረት ጀመረ።