የጸጥታ መዋቅሩ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል።

4

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) ​በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን እና ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታውቋል።

የመምሪያው ኀላፊ ይኸነው አበባው እንደገለጹት በከተማዋ የታየውን ሰላም ለማስቀጠል ከተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እና ከኅብረተሰቡ ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዚህም የከተማዋ ጸጥታ በመሻሻሉ የልማት ሥራዎች ያለምንም ሥጋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

​ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሰው ኀይልን በማደራጀት፣ ወታደራዊ ብቃትን እና ሥነ ምግባር በማሳደግ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።

የጸጥታ ሥራው በከተማው መዋቅር ብቻ ሳይወሰን ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በቅንጅት እየተመራ መኾኑን ነው የጠቀሱት ኀላፊው።

በምርጫ ጣቢያዎች እና ቀጠናዎች ላይ ጠንካራ ጥበቃ እንዲኖር እንዲሁም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ሙሉ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ይመራኛል ያለውን ፓርቲ በነፃነት እንዲመርጥ ለማስቻልም የጸጥታ መዋቅሩ ከሕዝቡ ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

​የከተማው የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላት ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠንቀቅ እና በቁርጠኝነት እየሠሩ መኾናቸውን ነግረውናል።

የተለያዩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳቸውን በነፃነት እና በሕጋዊ መንገድ እንዲያካሂዱ የሕግ ማስከበር ሥራው በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላት በሰላም ማስከበር ተግባሩ ሀገርን ለማስቀጠል የተሰጣቸውን ተልዕኮ በጽናት እየተወጡ መኾኑንም አንስተዋል።

ማኅበረሰቡ በሐሰተኛ ወሬዎች ሳይደናገር ዕውነታውን ተረድቶ የዜግነት መብቱን እንዲጠቀምም እየተሠራ ነው ብለዋል።

#አሚኮ #ዜና #7ኛው_ምርጫ #ደብረማርቆስ #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🗳️🇪🇹ለምርጫው ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
Next articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ በራራውን አደረገ።