🗳️🇪🇹ለምርጫው ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

3

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ሥራ አሥፈጻሚ እና የሴቶች ጉዳይ ኀላፊ አይሻ ያሲን እንደገለጹት ፓርቲያቸው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው።

በሂደቱም ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በሠለጠነ መንገድ እየተካሄደ የሚገኘውን የምርጫ ቅስቀሳ እና ክርክርም ሕዝቡ የፓርቲዎችን ሀሳብ ሰምቶ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል። ለቀጣይም ትልቅ ትምህርት እንደሚወሰድበት ጠቁመው በሂደቱም ደስተኛ መኾናቸውን አንስተዋል።

ፓርቲያቸው ሕዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍ እና ለሀገር የሚበጀውን ፓርቲ እንዲመርጥ የማድረግ ኀላፊነቱን እየተወጣ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ሁሌም ሰላምን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ምርጫው ስኬታማ እንዲኾንም የሚጠበቅበትን እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አስተባባሪ ኃይለማርያም ብርሀኑ በክልሉ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ የተሻለ ስለመኾኑ ተናግረዋል። በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር በውይይት እየተፈቱ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

ሕዝቡ በችግር ውስጥም ኾኖ የምርጫ ካርድ ማውጣቱን የገለጹት አቶ ኃይለማርያም በምርጫው ወቅትም የያዘውን ካርድ በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ እና አንድ ካርድ ዋጋ እንዳላት በአግባቡ በመገንዘብ ድምጹን እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በድሕረ ምርጫ ወቅት መንግሥትም ኾነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሕዝቡን ድምጽ ማክበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ችግር ሲያጋጥም ቅሬታዎችን በምርጫ ቦርድ ሕጉ መሠረት እስከ ፍርድ ቤትም በመሄድ ማቅረብ እንደሚቻል አንስተዋል። ለምርጫው ስኬታማነትም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበት ነው ሀሳባቸውን የሰጡት።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

#አሚኮ #ምርጫ2018 #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“አዲስ አበባ ላይ የተሠራው ሼል ኢትዮጵያን የመቀየር ጉዞ ማሳያ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየጸጥታ መዋቅሩ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል።