“አዲስ አበባ ላይ የተሠራው ሥራ ኢትዮጵያን የመቀየር ጉዞ ማሳያ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

5

 

አዲስ አበባ፡ ግንቦት 07/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) ከጠንካራ እሳቤ ወደተጨባጭ ስኬት በሚል መርህ በአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት እና ለውጥ ላይ የሚያጠነጥን “አዲስን እንደ አዲስ”የተሰኘ በውጭ ሀገር ደራሲያን የተፃፈ መጽሐፍ ተመርቋል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ማድረግ፤ የሀሳብ ፖለቲካ የሚንፀባረቅባት እና ለሕዝቦቿ ምቹ የኾነች ከተማ የማድረግ ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በትኩረት እየሠራባቸው የሚገኙ ቀዳሚ ጉዳዮች ናቸው።

“አዲስን እንደ አዲስ” የተሰኘውን መጽሐፍ ከደረሱት ውስጥ አንዱ ፕሮፌሰር ስሞን ሊ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጡ እና በተለይም አንድነትን የሚያሳዩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች የተሠሩባት ከተማ ኾና በማየታችን ደስተኞች ነን ብለዋል። ከዚህ ቀና ዕይታ በመነሳትም ይህንን መጽሐፍ ልንጽፍ ችለናል ነው ያሉት። ታሪክን በማስቀመጣችንም በሥራችን ደስ ብሎናል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባን ለማልማት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። በተለይም ሥራዎቹ መላው የከተማውን ሕዝብ በማስተባበር የተገኙ ውጤቶች መኾናቸው አንስተዋል።

አዲስ አበባ ከተማን ሕንጻዎቿን ማሳመር ብቻ ሳይኾን አምራች ከተማም እንድትኾን እና ዜጎች በዘመናዊ ግብርና ተሰማርተው ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ማድረግ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

በከተማዋ የተለያዩ የስበት ማዕከሎች፣ የታሪክ እና የቱሪዝም መዳረሻዎች በመገንባት ከተማዋን እንደስሟ ውብ ለማድረግ በተሠራው ውጤታማ ሥራ ከአፍሪካ 10 ጽዱ ከተሞች አንዷ እንድትኾን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ዛሬ የተመረቀው መጽሐፍም የትልቅ ሥራችን ማረጋገጫ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደሀገር የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ፤ የከተሞችን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይሩ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለዘመናት ወደ ኋላ ያስቀራት ዋነኛው ምክንያት የፖለቲካ ባሕል ስብራት መኾኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት ከዚህ እሳቤ በመውጣት እንደሀገር በተሠራው ኢትዮጵያን የመቀየር ጉዞ የአንድን ትውልድ የማይበገር የጽናት ተምሳሌት በጉልህ የሚያሳይ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

“አዲስ አበባ ላይ የተሠራው ሥራ እንደሀገር ኢትዮጵያን የመቀየር ጉዞ አንዱ ማሳያ ነው” ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው መጽሐፍ ከተሠራ ለውጥ እንደሚመጣ ያሳየ፣ እንደሀገር የምንኮራበት እና አጠናክረን የምናስቀጥለውን የለውጥ ጉዟችንን በግልጽ ያሳየ ነው፤ ሁላችንም ልንኮራበት እና በቀጣይ ሥራዎቻችንን የበለጠ ማጠናከር እንዳለብን ታላቅ ስንቅ ኾኖናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ

#አሚኮ_ዜና #የመጽሐፍምረቃ #አዲስአበባ #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየቅርሶች መመለስ ትውልዱ የራሱን ታሪክ እንዲጽፍ ያነሳሳሉ።