ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር እና ግብይት የሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።

7
​ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጋር በሕገ-ወጥ የነዳጅ ምርቶች ዝውውር እና ግብይት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ መንግሥት እያደረገ ያለውን የነዳጅ ድጎማ መነሻ በማድረግ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመግታት ልዩ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በሕገ ወጥ ድርጊት የተሠማሩ አካላት ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ለማድረግ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልጸዋል።
በሕገ-ወጥ ተግባሩ በቀጥታም ኾነ በተባባሪነት የተሳተፉ 170 ግለሰቦች ላይ የገንዘብ መቀጮ እና አሥተዳደራዊ ቅጣቶች ተጥለዋል ነው ያሉት።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 59 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነዳጅ የተያዘ ሲኾን ከየካቲት ወር ወዲህ ብቻ 33 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥል ነው ያሉት።
​የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ደኅንነት ዋና መምሪያ አዛዥ ኮማንደር በቀለ አብየ የነዳጅ እጥረትን ሰበብ በማድረግ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከታሪፍ በላይ ጭማሪ ባደረጉ 4 ሺህ 600 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዶ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መኾኑን ነው ያስረዱት።
አንዳንድ አሽከርካሪዎች መደበኛ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ወደ ኮንትራት ሥራ ማድላታቸው እና ለጥቁር ገበያ ቅድሚያ መስጠታቸው ለሕዝብ እንግልት ምክንያት ኾነው እንደነበር አውስተዋል።
​ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውሩን ለመከላከል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚዘልቅ የጋራ ቁጥጥር እየተደረገ ሲኾን ማኅበረሰቡ ሀገርን የሚጎዱ መሰል ተግባራትን በማጋለጥ እና ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ኀላፊነታችንን እንወጣለን።
Next articleበሆርሙዝ ሰርጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት እያደረገች መኾኗን ኢራን ገለጸች።