
ባሕርዳር፡ ግንቦት 07/2018ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
በምክክሩ ብልጽግና ፓርቲ ባለፋት ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት፣ አሁን ላይ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች፣ መጭውን ምርጫ ተወዳድሮ ከተመረጠ ትኩረት አድርጎ የሚሠራባቸው ጉዳዮች፣ ፕሮግራሞች እና ፖሊሲዎች ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገር መጽናት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም መመካከር እንደሚያስፈልግ ነው የጠቀሱት። ዛሬ የተደረገው ምክክርም የዚሁ አካል እንደኾነ ነው የገለጹት።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የተለየ አውድ ያለበት እንደኾነም ተናግረዋል።
ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና ምርጫው ሰላማዊ እንዲኾን የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን እንፈልጋለን ነው ያሉት። ለዚህም ከምርጫው በፊት እና ከምርጫው በኋላ የመምከር እና የማስተማር ኀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት። በምርጫ የሚመረጠው ፓርቲም ለሀገር ሰላም እና ፍቅር ይዞ የሚመጣ እንደሚኾን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሀገር ጉዳይ ሁልጊዜም ለወጣቶች አርዓያ መኾን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያውያን ለሀገር ሲሉ አንድነትን አስጠብቀው ለተተኪው ትውልድ ሊያስተላልፉ እንደሚገባም መክረዋል።
ዘጋቢ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
