ተጽዕኖ ፈጣሪ የኾኑ የሕዝብ እንደራሴዎችን መምረጥ ለጠንካራ ሀገር መሠረት ነው።

2
ደብረ ማርቆስ: ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያለ ሕዝብ ተወካይ ሀገር አይመሠረትም ብለዋል። ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለሕዝቡ የሚበጀውን እውነተኛ መሪዎች በመምረጥ በሰላማዊ ምርጫ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በከተማው የአውሮፕላን ማረፊያ እና ሌሎች የተሠሩ መሠረተ ልማቶች የሚያስመሰግኑ እንደኾኑም አንስተዋል። መሪዎችን በመደገፍ ወደ ኋላ የቀሩ እና ምላሽ ያላገኙ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ለሰላም መስፈን እንሠራለን ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ለሰላም እና ልማት እያደረገ ባለው ትብብር የከተማዋ ልማት እንዲፋጠን ማድረጉን የተናገሩት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ናቸው።
ከተማ አሥተዳደሩ በፈተና ውስጥም ኾኖ ሕዝቡን በልማት ተጠቃሚ እያደረገ ነው ያሉት ከንቲባው በቀጣይም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በመምረጥ የተጀመሩ ልማቶችን እንዲፋጠኑ ማኅበረሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ማኅበረሰቡ አሁንም በከተማዋ እየታዩ ያሉ ጥፋቶችን በመገሰጽ እና በመተባበር የከተማዋ እድገት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ መሥራት አለበት ነው ያሉት።
በዕለቱ የተገኙት የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ምርጫ ሰላም እና ልማትን በማረጋገጥ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ለማቋቋም ወሳኝ መንገድ ነው ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አሁንም የታጠቁ ኃይሎች የሰላም መንገድን እንዲቀበሉ በመምከር እና ለሰላም እንቅፋት የኾኑ ከፋፋይ እና አጥፊ አካሄዶችን በማውገዝ ለሁለንተናዊ እድገት በጋራ ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መከበር እና ለሰላም ሕዝቡ እያሳየ ያለው ተሳትፎ መልካም መኾኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ በተሳሳተ መንገድ የሚሄዱ አካላትን በማረም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለክልሉ ዕድገት ተፅዕኖ ፈጣሪ የኾኑ የሕዝብ እንደራሴዎችን በንቃት መምረጥ አለባቸው ብለዋል።
ሰላም ያለው በእያንዳንዱ ሰው አዕምሮ ውስጥ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ባለፉት ዓመታት በግጭት ውስጥ ኾኖም በርካታ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተው ወደ ሥራ የተገባበት እንደነበርም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleበደብረታቦር ከተማ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ቃል ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተካሄደ።
Next articleምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ኀላፊነታችንን እንወጣለን።