ቤተሰብ መልካም ትውልድ እና ሀገርን ለመገንባት ምሰሶ ነው።

3
አዲስ አበባ :ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሄልፕኤጅ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዓለም አቀፉን የቤተሰብ ቀን በተለያዩ ሁነቶች አክብሯል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሁሪያ አሊ ቤተሰብ ትውልድ የሚቀረጽበት ቀዳሚው ትምህርት ቤት መኾኑን ገልጸዋል። ቀኑ ሲከበር ለቤተሰቦቻችን ተገቢውን ምሥጋና እና ክብር በመስጠት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
መልካም ትውልድ እና ሀገርን ለመገንባት ቤተሰብ እንደ ምሰሶ ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
መሥሪያ ቤቱ ቤተሰብ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችል የቤተሰብ አሥተዳደር ክህሎት የትምህርት ማንዋል እና የቤተሰብ ጥበቃ የድርጊት መርሐ-ግብር አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።
በዕለቱ የኅብረተሰብ እና የሀገር መሠረት የኾነው ቤተሰብ መልካም እሴትን መገንባት እና የትውልድ ትስስር በመፍጠር ረገድ ሊኖረው ስለሚገባው ሚና የሚያትት ሰነድ ቀርቧል።
ሰነዱ ከቤተሰብ ምሥረታ ጀምሮ እስከ ጥንዶች አረጋውያን ዘመን ድረስ ያሉ ሂደቶችን በስፋት የተነተነ ነው። በተለይም በቤተሰብ ተኮር አዳዲስ ልማዶች፣ በዲጂታል አጠቃቀም ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
ዘጋቢ:- ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እስካሁን ስኬታማ ሥራዎችን ሠርቷል።
Next articleበደብረታቦር ከተማ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ቃል ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተካሄደ።