
ባሕር ዳር :ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፍተኛ የፌደራል፣ የክልል የሥራ ኃላፊዎች እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የአፈጻጸም ሪፖርቱን ዛሬ ጠዋት አቅርቧል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ዐበይት ተግባራት፣ የገጠሙትን ተግዳሮቶች እና ለተግዳሮቶቹ የሰጣቸውን መፍትሔዎች አንስቷል። ወደፊትም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በታሰበው ልክ ለማስኬድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ሚናዎችን አስቀምጧል።
በእስካሁን ሥራ ከቀረቡት ቁልፍ ስኬቶች መካከል:-
አካታች እና አሳታፊ የኾነ የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ
የሀገራችንን 93 በመቶ የሸፈነ በ1234 ወረዳዎች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ ማድረግ ይገኙበታል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ 22 ዙር የሚኾን ከተለያዩ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመመካከር የተደረገበት ሰፊ ጥረት ቢኖርም ባለው ምቹ ያልኾነ ሁኔታ በትግራይ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ምክክር ለማድረግ አለመቻሉን አመልክቷል።
ለዚህ ተግዳሮት ምላሽ ለመስጠትም ኮሚሽኑ ከመላው የትግራይ ክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆችን በማካተት በአዲስ አበባ ከተማ በማሰባሰብ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ ማካሄዱን ገልጿል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቀጣዩ የሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ ኮሚሽኑ የሚከተሉትን ተግባራት ለማካሄድ አስቀምጧል:-
የፖለቲካ ተዋንያንን ተሳትፎ ማጠናከር
የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን መቅረፅ
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤን ማካሄድ
በሀገር ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን ውጤቶች እና ምክረ ሀሳቦች ተፈፃሚነት ማመቻቸት የሚሉት የኮሚሽኑ ቀጣይ ሥራዎች መኾናቸው ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
