
ባሕር ዳር :ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ባለፉት ዓመታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱ ወደፊት እንዲራመድ በትዕግስት እና ከፍ ባለ የሞያ ስነ ምግባር በማከናወን አሁን ያለበት ምዕራፍ ያደረሱትን ሁሉንም ኮሚሽነሮች አመሰግናለሁ ብለዋል።
የምክክር ባሕል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ ነው። ጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ባሕል ግንባታ ደግሞ ያላሰለሰ የመነጋገር ልምምድ እና የሰከነ የወል መደማመጥን ግድ ይላል ነው ያሉት።
የእስካሁን ሂደቱም በማኅበረሰባችን በየደረጃው የመደማመጥን ከፍ ያለ ጠቀሜታ አሳይቷል። ሂደቱ በሀገራችን ሁሉም ማዕዘናት የሚገኙ ከ90 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያንን አመለካከቶች እና የውይይት ውጤቶች ያንፀባረቀ ኾኗል ብለዋል።
ለሀገር ወሳኝ ፋይዳ የያዘው የምክክሩ ምዕራፍ ተጨባጭ ውጤት ወደሚያስገኘው ቀጣይ ምዕራፍ በሚሸጋገርበት በዚህ ወቅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት እና ዘላቂ መረጋጋትን የሚያረጋግጥ የጋራ ፅኑ አቋም እና ገንቢ በኾነ መንገድ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
