የሀገር ሰላም አምባሳደሮች ኾነን ምርጫውን ማስኬድ አለብን።

5
🇪🇹
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫ ወቅት የማኅበረሰብ ሚና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር መረጋጋት እጅግ ወሳኝ ነው። ማኅበረሰቡ ከመምረጥ ባለፈ በርካታ ኀላፊነቶችም አሉበት።
የደብረ ማርቆስ ነዋሪ የኾኑት ጌታሁን ፈንቴ ምርጫ የአንድ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት እንዲኖረው ሕዝቡ ካርድ አውጥቶ ሰላማዊ በኾነ መንገድ በምርጫ ሂደት መሳተፍ እንደሚኖርበት ተናግረዋል።
ከቅድመ እስከ ድኅረ ምርጫ ድረስ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲኖር እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ሀገር ያለ ሰላም ትርጉም አልባ ስለኾነች ሰላምን የምንሰብክ አምባሳደሮች መኾን ይጠበቃልም ብለዋል። ለዚህም ከራስ አልፎ በቅርበት የሚያውቋቸውን ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች እያስገነዘቡ እንደኾነ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ ነዋሪው ጫኔ መንገሻ ደግሞ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በተካሄዱ ምርጫ ሂደቶች ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸውልናል።
ምርጫ 2018 ሰላማዊ ስኬታማ እንዲኾን በአካባቢው ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች ሰዎች ግንዛቤ እየፈጠሩ እንደኾነ ገልጸዋል። ሰላም ሲኖር እድገት፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እንደሚኖርም ጠቅሰዋል።
ሌላው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ ሀገሪቱ መሪ ስለሚያስፈልጋት ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ እርሳቸው ሰላማዊ ኾነው አካባቢያቸው ሰላም እንዲኾን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸውልናል። ሰው ለሰው ፍቅር መስጠት አለበት፤ ለሀገር ቀጣይነትም ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል ነው ያሉት። የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲኾን ማኅበረሰቡን ጨምሮ መንግሥት እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲኖራቸውም መክረዋል።
በምርጫው ሂደት በንቃት መሳተፍ፤ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ መስጠት፤ ሰላምን እና ደህንነትን ማስጠበቅ፤ የምርጫ ሂደቱን መታዘብ እና መከታተል እና ከምርጫ በኋላ ያለውን ውጤት በጸጋ መቀበል ከማኅበረሰቡ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላማዊ የምርጫ ሥርዓት ለዴሞክራሲ መሠረት ነው።
Next articleተመካክሮ፣ ተወያይቶ እና ተግባብቶ ሀገርን ማሻገር ያስፈልጋል።