
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ምሰሶ ነው።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ሀሳቡ ተስፋ የምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሕዝብ ድምጽ የተመረጠ ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ መኾኑን ገልጸዋል። ያልተመረጠው ፓርቲ ደግሞ ለተመረጠው የፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣኑን በሰላም ሲያስተላልፍ እንደኾነ ተናግረዋል።
ሰላማዊ ሽግግር ከሌለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለ ማለት እንደማይቻልም ገልጸዋል። ሰላማዊ የምርጫ ሥርዓት ለዴሞክራሲ መሠረት እንደኾነም አንስተዋል።
ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ከሌለ፣ ሥልጣንን በጉልበት ለመያዝ እና ለማቆየት የሚደረግ እንቅስቃሴ የሕዝብ ፍላጎት አለመኾኑንም ተናግረዋል።
በሕዝብ ፍላጎት ያልመጣ የመንግሥት ሥርዓት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ነው ማለት እንደማይቻል ነው የጠቀሱት።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለ ሰላማዊ የምርጫ ሂደት ሊታሰብ እና ሊሳካ እንደማይችልም ገልጸዋል። “ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታም ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ እንደኾነ” አስረድተዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ምሁሩ ልማት፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የታለመላቸውን ዓላማ ሊያሳኩ የሚችሉት ሰላም ሲኖር ብቻ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ለዚህም ገዥው ፓርቲም ኾነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላም ባለቤት ሊኾኑ እንደሚገባ መክረዋል። የጋራ ርብርባቸውም ሰላምን ሊያጸናው እንደሚችል ገልጸዋል። ሰላም በብዙኃኑ ፍላጎት እና ምኞት ብቻ የሚመጣ ስላልኾነ ከሁሉም አካል ተግባራዊ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሰላማዊ አማራጭ፣ መምረጥ እና ሰላማዊ አካሄድ መከተል ሰላም እንዲጸና፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እድገት እንዲኖር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከወዲሁ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
የምርጫ ቦርድ ሕጎችን እና መመሪያዎችን መከተል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በቀጣይም በሕጉ መሠረት የተፈጸመን የምርጫ ውጤት በጸጋ መቀበል እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። ይህም የዴሞክራሲ አንድ መርህ እንደኾነ ነው ያነሱት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
